የህጻናት ዓይነ ስውርነት (Childhood Blindness)

የህጻናት ዓይነ ስውርነት (Childhood Blindness)

በዶ/ ሙሉሰው አስፈራው። በሮሃ ስፔሻላይዝድ ዐይን ሕክምና ክሊኒክ፣ የህጻናት ዓይን ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም።

ትርጉም

የህጻናት ዓይነ ስውርነት የሚባለው ዕድሜያቸው ከ 16 ዓመት በታች በሆኑ ህጻናት ላይ የቀጥታ እይታ ልኬት ከሁለት አይኖቻቸው በተሻለ የሚያየው ዓይን ላይ ከ 3 በ 60 (3/60) በታች ሲሆን ነው፡፡

3/60 እይታ ማለት ጤነኛ ዓይን ያለው ሰው በ 60 ሜትር ርቀት ላይ ሆኖ የሚያየውን  ፊደል/ ምልክት ታካሚው በ3 ሜትር ብቻ ማየት ሲችል ነው፡፡ይህም የዕይታ ችሎታው ምን ያህል እንደቀነሰ ያሳያል፡፡

 

የችግሩ ስፋት/መጠን

በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.26 ሚሊዮን ህጻናት ዓይነ ስውራን ሲሆኑ፤ በእያንዳንዱ ደቂቃ አንድ ህጻን ዓይነ ስውር ይሆናል፡፡ (በየዓመቱ 500,000 ዓይነ ስውራን ህጻናት ይጨመራሉ)

በኢትዮጵያ ከ1000 ህጻናት  ውስጥ አንድ ህጻን ዓይነ ስውር ሲሆን በአጠቃላይ ከ 50,000 – 60,000 ዓይነ ስውራን ህጻናት እንዳሉ ይገመታል፡፡

የህጻናት ዓይነ ስውርነት የሚያስከትሉ የዓይን ችግሮች/በሽታዎች

በቀላሉ በመነጽር ከሚስተካከሉ የእይታ ችግሮች ጀምሮ በቪታሚን ኤ እጥረትና ዓይን ውስጥ በሚፈጠሩ ኢንፌክሽኖች  እስከ በውልደት ጊዜ ጀምሮ የሚፈጠሩ የዓይን ችግሮች ድረስ በተለያዩ ምክንያቶች ዓይነ ስውርነትን ያስከትላሉ፡፡

ዋና ዋና መንስዔዎች የሚከተሉት ናችው፡-

    • ፩. በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የእይታ ችግር ( Refractive error)
    • ፪. የዓይን ሞራ (cataract)
    • ፫. በተለያየ ምክንያት የሚከሰት የዓይነ መስታወት ጠባሳ ( በተለይም የቪታሚን ኤ እጥረት፤ ኩፍኝ፤ የዓይነ መስታውት ቁጣ/ምርቀዛ…ወዘተ)
    • ፬. የዓይን ግፊት ህመም (Glaucoma)
    • ፭. እይታ ነርቭ ችግር (Optic atrophy)
    • ፮. የእይታ አንጎል ላይ የሚፈጠሩ ችግሮች (Cerebral visual impairment)
    • ፯. ያለ ጊዜው ቀድመው በሚወለዱ ጨቅላ ህጻናት ላይ ረቲና ውስጥ የሚፈጠር ችግር [Retinopathy of Prematurity (ROP)]
    • ፰. ከውልደት ጀምሮ የሚፈጠሩ የዓይን በሽታዎች (congenital malformations)

በህጻናት ላይ የዓይን ችግሮችን እንዴት መለየት እንችላለን?

በኢትዮጵያ ከ80 በመቶ በላይ ዓይነ ስውርነትን የሚያስከትሉ በሽታዎችን አስቀድሞ በመከላከል ወይም በህክምና ማስወገድ የምንችላቸው ናቸው፡፡

ይኸውም አስቀድሞ በጊዜው ( በተለይም ህጻናት የዓይንና አንጎል እድገት ላይ ባለበት ከ8 ዓመት በፊት) ችግሩን በመለየትና አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ ነው፡፡

ነገር ግን የአብዛኛዎቹ ህጻናት ዓይን ችግር የሚታወቀው በትምህርት ቤት ውስጥ በሚያሳዩት የዕይታ ችግር በመምህራኖቻቸው ሲሆን ይህም ዉጤታማ ህክምና ለማድረግ በጣም የዘገየ ሊሆን ይችላል፡፡

ስለሆነም ወላጆች/አሳዳጊዎች አስቀድመው፤

    • ፩. የህጻናትን ዓይን በማየትና
    • ፪. በሚያሳዩት ባህርይ የዓይን ችግር መኖሩን መለየት ይችላሉ፡፡

በህጻናት ዓይን ላይ ችግር ስለመኖሩ ጠቋሚ ምልክቶች፡-

    • ፩. በዓይን ዉሰጥ መሃል ላይ ነጭ ነገር/ነጥብ መታየት
    • ፪. መጫወቻ አሻንጉሊት/ብርሃን ወይም የሰውን ፊት አተኩሮ አለማየት እና የሚንቀሳቀሱ ነገሮችን በዐይናቸው አለመከተል ( በጨቅላ ህጻናት ላይ የእይታ መቀነስ ምልክት ነው)
    • ፫. አንዱ ወይም ሁለቱም ዓይኖች መጠን ከመደበኛ በታች ትንሽ ወይም ትልቅ መሆን
    • ፬. ሸውራራ ዓይን
    • ፭. የዓይን ቅላት
    • ፮. የዓይን ውስጥ እብጠት /ቁጣ/ምርቀዛ
    • ፯. አብዝቶ በተደጋጋሚ እንባ መፍሰስ
    • ፰. ዓይነ መጎልጎል (Proptosis)

ህጻናት  የሚያሳዩትን  የባህርይ  ለዉጥ በማጥናት የዓይን ችግር መኖሩን መለየት

    • ፩. ጨቅላ ህጻናት 3 ወር እድሜ ሲሞላቸው የሰው ፊት ላይ ካላተኮሩና ፈገግታ ካላሳዩ
    • ፪. ህጻናት አተኩረው ሲያዩ አንድ ዓይናቸውን የሚሸፍኑ ከሆነ
    • ፫. ሲያነቡ ወይም የሚያዩትን ነገሮች ወደ ፊታቸው የሚያቀርቡ ከሆነ ወይም ወደ ቴሌቪዥን፤ ኮምፒዩተር፤ ሰሌዳ በጣም ቀርበው ብቻ የሚያዩ ከሆነ
    • ፬. አተኩረው ሲመለከቱ ፊታቸውን ወደ አንድ አቅጣጫ የሚያዞሩ ወይም ጭንቅላታቸውን የሚያገድሉ ከሆነ
    • ፭. እድሜያቸው ከፍ ያሉ ህጻናት ደግሞ የሚያዩት ነገር ደብዛዛ ነው ወይም ለማየት ተቸግሬለሁ ብለው ከተናገሩ
    • ፮. በትኩረት ሲመለከቱ ወይም ከሩቅ በሚያዩበት ጊዜ የዓይን ቆብ አጥብበው የሚያዩ ከሆነ
    • ፯. የሚያዩት ነገር ደርቦ / ሁለት ሁለት ሆኖ መታየት
    • ፰. ዓይነ ዥዋዥዌ (ከቁጥጥር ውጪ የሆነ የዓይን እንቅስቃሴ)
    • ፱. በተደጋጋሚ ዓይናቸውን ማሸት/ማሳከክ ሲኖር

ወላጆች/አሳዳጊዎች የህጻናትን ዓይን ጤና ለመጠበቅ ምን ማድረግ አለበቸው?

    • የህጻናትን የእጅና የፊት ንጽህና መጠበቅ
    • ክትባት በወቅቱ ማስከተብ (በተለይም የኩፍኝ ክትባት)
    • የተመጣጠነ ምግብ መመገብ (በተለይም አትክልትና ፍራፍሬ በቪታሚን ኤ የበለጸጉ ምግቦችን እንደ ካሮት፤ ማንጎ፤ አቮካዶ፤ አረንጓዴና ሰፋፊ ቅጠላ ቅጠል ያላቸውን)
    • የህጻናት ዓይን ላይ ችግር መኖሩን ከጠረጠሩና  ጠቋሚ ምልክቶችን ካዩ ሳይዘገዩ ወዲየውኑ ወደ ዓይን ሕክምና ተቋም በመውሰድ ማስመርመር ያስፈልጋል፡፡
    • የህጻናትን ሕክምና መዘገየትን ማስወገድ በጣም አስፈላጊ ነው፡፡
    • የሐኪም ምክር በተገቢው መፈጸም ወሳኝ ነው፡፡
    • መደበኛ ክትትል ሳያቋርጡ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በህክምና ተቋም የሚደረጉ ምርመራዎች የሚከተሉት ናቸው፡፡

    • የእይታ ልኬት ይደረጋል
    • የመነጽር ልኬት (ህጻናት ሲሆኑ የዓይን ጠብታ በመጨመር የሚደረግ ምርመራ)
    • የዓይን ዉጪና ውስጥ ምርመራ
    • እንደችግሩ ዓይነት ደግሞ ሌሎች ተጨማሪ ምርመራዎች (ለምሳሌ፡ አልትራሳውንድ፤ CT scan/MRI) ማድረግ ሊያስፈልግ ይቻላል፡፡
    • ሙሉ ምርመራ ለማድረግ የማይተባበሩ ህጻናት ከሆኑ ደግሞ የሰመመን (ማደንዘዣ) መድኃኒት በመስጠት የሚደረግ ምርመራ

ሕክምናው

    • እንደ ችግሩ ዓይነትና ደረጃ የተለያየ ሲሆን፡-
      • የመድኃኒት ሕክምና
      • የመነጽር ሕክምና
      • አንድ ዓይን ለተወሰነ ጊዜ በመሸፈን ስንፈተ ዕይታን ማስተካከልና
      • የቀዶ ጥገና ሕክምና ሊሆን ይችላል

ጤነኛ  ህጻናትን መቼ መቼ የዓይን ምርመራ ማድረግ ያስፈልጋል?

    • በወቅቱና በጊዜው መታከም ያለባቸው አስቀድመው ያልታወቁ የዓይን ችግሮች/በሽታዎች የህጻናት ዓይነ ስውርነትን ሊያስከትሉ ይችላሉ፡፡
    • በመሆኑም አስቀድሞ በወቅቱ ችግሮችን በማወቅና በመለየት መቅረፍና ዓይነ ስውርነትን መከላክል ይቻላል፡፡
    • ይኸውም መደበኛ የዓይን ምርመራ በማድረግ ነው፡፡

የመጀመሪያ  የዓይን  ምርመራ መቼ መደረግ አለበት?

    • አንድ አመት እድሜ ላይ ፤ ከዚያ መዋለ ህጻናት(KG) ከመግባታችው በፊት

በአጠቃላይ፡

    • ከልደት – 2 ዓመት ዕድሜ ፤ የመጀመሪያ ምርመራ በ 6 – 12 ወር ዕድሜ ላይ
    • ከ 3 – 5 ዓመት ዕድሜ ፤  ቢያንስ አንድ ጊዜ ማስመርመር
    • ከ Childhood BlindnessChildhood Blindness 6 – 17 ዓመት ዕድሜ፤  አስቀድሞ 1ኛ ክፍል ከመግባታቸው በፊት፤ ከዚያ በዓመቱ ማስመርመር ያስፈልጋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *