በህጻናት ላይ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ችግር (Refractive Error)

በህጻናት ላይ በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ችግር (Refractive Error)

በዶ/ ሙሉሰው አስፈራው። በሮሃ ስፔሻላይዝድ ዐይን ሕክምና ክሊኒክ፣ የህጻናት ዓይን ሕክምና ስፔሻሊስት ሐኪም።

በዓይናችን  እንዴት  እናያለን?

በጤነኛ ዓይን ከሚታዩ ነገሮች ላይ አርፎ ያንጸበረቀው ብርሃን፡ ወደ ዓይን ውስጥ ይገባና በሌንስና (lens) በዐይን መስታዋት (cornea) የተቀናጀ የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል  አማካኝነት ብርሃኑ ተነጣጥሮ ሪቲና (የዓይን የውስጥ ግድግዳ) ላይ በትክክል ያርፋል፡፡

ይህ በሪቲና ላይ ያረፈው ምስል ደግሞ በእይታ ነርቭ (optic nerve) አማካኝነት ወደ እይታ አንጎል ክፍል (Visual cortex) ሲደርስ ይህ የአንጎል ክፍልም የሚታየው ነገር ምን እነደሆነ ይተረጉምና አካባቢያችንን እንድናይና እንድንረዳ ያችላል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ 2/3ኛውን የዓይን ብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል በዐይን መስተዋት የሚከናወን ሲሆን ቀሪውን 1/3ኛው ኃይል ደግሞ በሌንስ አማካኝነት ይደረጋል፡፡ ይልቁንም እንደ ማንበብ የመሰሉትን የቅርብ እይታ በሚያስፈልግበት ጊዜ ሌንስ ቅርጹን በመቀየር የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል በመጨመር ምስሉ በሪቲና ላይ እንዲያርፈ በማድረግ ጥርት ያለ እይታ እንዲኖር ያደርጋል (ምስል ፩)፡፡

ምስል ፩  በዓይናችን እንዴት እንደመናይ

በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ችግር  የሚፈጠረው ወደ ዓይን ውስጥ የሚገባው ብርሃን በትክክል ሪቲና ላይ ሳያርፍ ሲቀር፡ በቅርብ፤ በሩቅ ወይም በቅርብም በሩቁም የምናያችው ነገሮች ደብዛዛ ሲሆኑ ነው፡፡

የሚከሰተው የዕይታ ችግር ደረጃውና አይነቱ በተለያዩ ምክንያቶች የሚለያይ ሲሆን በዋናነት፡-

  • ፩) የዓይን ቅርጽና መጠን እና
  • ፪) የዓይን የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል፤ ለሚፈጠረው የእይታ ችግር አይነትና ደረጃ መለያየት አብይ ምክንያቶች ናቸው፡፡

ይህ የዕይታ ችግር በአገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የእይታ መቀነስ በማምጣት አንደኛ ደረጃ የሚጠቀስ ሲሆን ዓይነ ስውርነትን ከሚያመጡ ዋና ዋና የዓይን ችግሮች አንዱ ነው፡፡

በትምህርት ላይ ያሉ ልጆች ለዚህ ችግር ከፍተኛ ተጋላጭ ናቸው፡፡

ችግሩም የመማር ችሎታቸውን ከመቀነስ በተጨማሪ በአካላዊና አዕምሯዊ እድገታቸወ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ ያሳድራል፡፡

ልጆች ትምህርት ከሚቀስሙባቸው መንገዶች 80% የሚሆነውን የሚይዘው እይታ እንደሆነ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡

ዓይነቶች

በአጠቃላይ ፬ ዓይነት በመነጽር ሊስተካከሉ የሚችሉ የእይታ ችግሮች አሉ፡፡ እነዚህም፡-

  • ፩   በቅርብ የማየት ችግር (Hyperopia)
  • ፪   በርቀት የማየት ችግር (Myopia)
  • ፫   አጠቃላይ እይታ ብዥብዥታ(Astigmatism)
  • ፬   በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚመጣ በቅርብ የማየት ችግር (Presbyopia)

፩ በቅርብ የማየት ችግር

ይህ የዕይታ ችግር የሚከሰተው የዓይን ኳስ መጠን ትንሽና አጭር ሲሆን ወይም የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል አነስተኛ ሲሆን ነው፡፡

በቅርብ ከሚገኙ ነገሮች ተንጸባርቆ የመጣ ብርሃን ረቲናውን አልፎ ከረቲናው በስተጀርባ ያርፈል፡፡ በርቀት ካሉ ነገሮች ተንጸባርቆ የመጣው ብረሃን ከቅርብ ከመጣው በተሻለ ሁኔታ ረቲና ይደርሳል (ምስል 2)፡፡

በዚህም ምክንያት በርቀት የሚገኙ ነገሮችን ማየት ሲቻል በቅርብ ያሉ ነገሮች እይታ ደግሞ ያልጠራ (የደበዘዘ) ይሆናል፡፡

ምስል ፪  በቅርብ የማየት ችግር

ይህ ዓይነት የዕይታ ችግር በብዛት በዘር የሚተላለፍና ሲወለዱ ጀምሮ የሚኖር ችግር ሲሆን የልጆች ዓይን መጠን እያደገና እየጨመረ ሲሄድ በቅርብ የማየት ችግሩ እየቀነሰ ይሄደል፡፡

ልጆች ላይ የተከሰተው የእይታ መቀነስ ችግር አነስተኛ ከሆነ ችግሩን ለመቋቋም የሚያስችል ተፈጥሯዊ መሣሪይ ስላላቸው በቅርብ የሚገኝ ነገርን በሚያዩበት ጊዜ የእይታ መደብዘዝ ላያጋጥማቸው ይችላል፡፡

የችግሩ መጠን ከፍተኛ ከሆነ ግን የዕይታ ችግሩን በበቂ ሁኔታ በተፈጥሯዊ ማካከሻ ብቻ መቅረፍ ስለማይቻል የቅርብ እይታ የሚጠይቁ ሥራዎችን (ምሳሌ፤ መጽሐፍ ማንበብ) ለመስራት ከባድና ፈታኝ ይሆናል፡፡ የዓይን ጡንቻቸውን በከፍተኛ ሁኔታ በመጠቀማቸውም የዓይን ድካም (ዓይነ ስትራፖ) ስለሚፈጥር የሚከተሉ ምልክቶች ይኖራቸዋል፡፡

  • የዓይን ድካም ስሜት
  • በዓይን ዙሪያ ህመም መሰማት
  • የዓይን መቅላትና የማቃጠል ስሜት
  • ራስ ምታት/ህመም
  • ብርሃን መፍራት

እነዚህ ስሜቶች የልጆችን የቅርብ እይታ የሚጠይቁ ሥራዎችን የመሥራት ዝንባሌ ወይም ውጤታማነት ይቀንሳል፡፡ መፍትሄውም በማስገደድ እንዲያነቡ ከማድረግ ወይም ልጄ ማንበብ/ማጥናት አይወድም/አትወድም ከማለት ይልቅ ወደ ሕክምና ተቋማት በመውሰድ ማስመርመርና ሕክምና እንዲያገኙ ማድረግ ነው፡፡

ከፍተኛ የሆነ በቅርብ የማየት ችግር ያለባቸው ህጻናትና ልጆች ችግሩን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት በሚያደርጉት ጥረት ዓይን መንሸዋረር ይፈጠራል፡፡

፪ በርቀት የማየት ችግር

ይህ ዓይነት የእይታ ችግር የሚከሰተው መጠኑ ትልቅ የሆነ የዓይን ኳስ ሲኖር ወይም የዓይን የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል ከፍተኛ ሲሆን ነው፡፡

ከሚታየው ነገር ተንጸባርቆ የመጣው የብርሃን ጮራ በተፈለገው መጠን ረቲና ላይ አያርፍም፡፡ ይልቁንም ጮራው ረቲና ላይ ሳይደርስ ከረቲናው በፊት ያርፋል (ምስል ፫)፡፡

በዚህም ምክንያት በርቀት ያሉ ነገሮችን በሚያዩበት ጊዜ ያልጠራ (የደበዘዘ) እይታ ይከሰታል፡፡ በቅርብ ካሉ ነገሮች የሚመጣ ብርሃን በተሸለ ረቲና ላይ ያርፋል፡፡

ስለሆነም በቅርብ በደንብ ማየት ሲችል በርቀት ግን ለማየት መቸገር ይኖራል፡፡

ምስል ፫  በርቀት የማየት ችግር

ይህ ዓይነት የእይታ ችግር በዘር ሊተላለፍ የሚችል ሲሆን በብዛት ከ6-14 ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ይከሰታል፡፡በርቀት የማየት ችግር ከልጆች እድገት ጋር በተያያዘ እየተባባሰ ይሄዳል፡፡ ስለሆነም በየስድስት ወር ልዩነት የእይታ ክትትልና አስፈላጊ ከሆነም የመነጽር ቁጥር መቀየር ሊያስፈልግ ይችላል፡፡ ዕድሜ እየጨመረ ሲሄድ ግን በተለይም ከ20-40 ዓመት ባለው ጊዜ የእይታ ችግሩ ብዙ ለውጥ አያሳይም፡፡

ይህ ዓይነት የእይታ ችግር ያለባቸው ልጆች በትምህርት ቤት ውስት ከሰሌዳ ፊት ለፊት እንዲሁም በቤት ውስጥ ከቴሌቪዥን አጠገብ መቀመጥ ይመርጣሉ፡፡ በቅርብ የማየት ችሎታችው የተሻለ ስለሆነ ያለባቸው የእይታ ችግር በጣም ከፍተኛ ካልሆነ በስተቀር መጽሐፍ ወይም ደብተር ማንበብ ብዙም አይቸገሩም፡፡

ከፍተኛ የሆነ የርቀት የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ለብርሃን መቀበያ የዓይን ክፍል (ረቲና) መላቀቅ የተጋለጡ ናችው፡፡ ስለሆንም መደበኛ ዓይን መርመራና ክትትል ማድረግና የመላቀቅ ምልክቶች (የብረሃን ብልጭታ፤ ጥቃቅንና ጥቋቁር የሸረሪት ድር የሚመስሉ ነገሮችን ማየት፤ ድንገተኛ የእይታ አድማስ ከፊል ግርዶሽ) ከታዩ ወዲያዉኑ ወደ ሕክምና ተቋም መውሰድ ያስፈልጋል፡፡

፫ አጠቃላይ የዕይታ ብዥብዥታ (በቅርብ-በርቀት የማየት ችግር)

የዓይነ መስታወት (cornea) ቅርጽና ይዘት ከመደበኛው ወጣ ባለ መልኩ የተዛባ የክብ ቅርጽና ወጣገብነት ያለው ገጽታ ሲኖር የሚፈጠር የእይታ ችግር ነው፡፡

የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ሂደቱም በሁሉም የዓይነ መስታወት ክፍል ላይ ተመሳሳይ ስለማይሆን አቅጣጫ የቀየረው የብርሃን ጮራ የተለያየ መድረሻ ይኖረዋል፡፡ የተነጣጠረው የብርሃን ጮራ ከረቲና በፊት ወይም በስተጀርባ ያርፋል (ምስል ፬)፡፡

ምስል ፬  አጠቃላይ የዕይታ ብዥብዥታ

ስለሆነም በአጠቃላይ የቅርብና የርቀት እይታው የደበዘዘና የሚታየው ነገር የተዛባ ቅርጽና ገጽታ (ይዘት) ያለው ይሆናል፡፡

ይህ ችግር ያለባቸው ህጻናት ተማሪዎች ከሰሌዳው በመቅረብ ወይም በመራቅ የእይታ ችግሩን ማካካስ አይችሉም፡፡

አጠቃላይ የእይታ ብዥብዥታ አንዳንድ ጊዜ ብቻውን ወይም በቅርብ የማየት ችግር (Hyperopia) እና በርቀት የማየት ችግር (Myopia) ጋር ተደርቦ ይከሰታል፡፡

፬ በዕድሜ መግፋት ምክንያት የሚመጣ በቅርብ የማየት ችግር

እድሜ እየጨመረ ሲሄድ (በተለይም ከ40 ዓመት ጀምሮ) የተፈጥሮ ሌንስ እየጠነከረና ቅርጹንም የመቀየር ችሎታ እየቀነሰ ሲሄድ የዓይን ተፈጥሯዊ ኃይል የመጨመር ተግባር በመዳከሙ ምክንያት በቅርብ ያሉ ነገሮችን ለመለየት/ለማንበብ አስቸጋሪ ይሆናል (ለምሳሌ በመርፌ ቀዳዳ ክር ማስገባት፡ የሞባይል ካርድ መሙላት፡ ጥቃቅን ፊደሎችን ማንበብ  አለመቻል)፡፡

ሕክምናውም እነዚህን የቅርብ እይታ የሚያስፈልጉ ሥራዎችን በሚሰሩበት ጊዜ ማንበቢያ መነጽር መጠቀም ነው፡፡

በመነጽር ሊስተካከል የሚችል የዕይታ ችግር  ምልክቶች

በአብዛኛው የተለመደው ዋናው ምልክት የቅርበት፤ የርቀት ወይም የሁለቱም እይታ መደብዘዝ/ብዥታ ነው፡፡

ሌሎች ምልክቶች፡-

  • አተኩረው ሲያዩ የላይኛውና የታችኛው ዓይን ቆብ መካከል ያለውን ክፍት ቦታ በጣም አጥብቦ ማየት
  •  ራስ ምታት
  • የዓይን ጡንጫ ውጥረት መሰማት
  • እንድ ነገር ሁለት ሆኖ/ደርቦ ማየት
  • ሲያነቡ ወይም ኮምፒውተር ሲጠቀሙ  ለማተኮር መቸገር

ሕክምና

በባለሙያ የሚደረግ የዓይን ምርመራ ማድረግ (የእይታ መጠን ልኬትና ተያያዥ ችግሮችን ማወቅ)

ሕክምናው በዋናነት የመነጽር ሕክምና ወይም ተለጣፊ ሌንስ (contact lens) ማድረግ ሲሆን እንደችግሩ ደረጃና ዓይነት ደግሞ ቀዶ ጥገና ሊያስፈልገው ይችላል፡፡

የመነጽር ሕክምናው፡-

በቅርብ የማየት ችግር ላለባቸው የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል የሚጨምር ሌንስ ያለው መነጽር [ጨረር ሰብሳቢ ምስሪት – Plus (convex) lens]

በርቀት የማየት ችግር ላለባቸው የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል የሚቀንሱ [ጨረር በታኝ ምስሪት – minus (concave) lens]

አጠቃላይ እይታ ብዥብዥታ ላለባቸው ሰዎች የዓይን ብሌንን ገጽታዊ ብርሃን የማስተላለፍ ኃይል ልዩነት የሚያስተካክሉ ሌንሶች (cyclinderical lens)

የቀዶ ጥገና ዓይነቶች፡-

በጨረር (በሌዘር) የዓይነ መስታወትን ቅርጽ መቀየር

ዓይን ውስጥ ሰው ሰራሽ ሌንስ ማስገባት

የተፈጥሮ ሌንስ በማውጣት የዓይንን የብርሃን አቅጣጫ የማስቀየር ኃይል መቀነስ ናቸው፡፡

በመነጽር መታከም የሚችሉ የዕይታ ችግሮች የሚያስከትሏችው ተዛማጅ የዓይን ጤና ችግሮች

፩ ሰነፍ ዓይን (Amblyopia/ lazy eye)

ይህ ዓይነት እይታ መቀነስ አንጎል በቂ መረጃ ከማያቀብል ዓይን ጋር ያለውን ግንኙነት በማቋረጡ ምክንያት የሚከሰት ስንፈተ እይታ ነው፡፡

ከመካከለኛ እስከ ከፍተኛ በመነጽር የሚስተካከል የእይታ ችግር ባለባቸውና ወቅታዊና ተገቢ ሕክምና ካለገኙ ህጻናትና ልጆች (በተለይም ከ8-9 ዓመት ዕድሜ በታች) ላይ የሚከሰት የእይታ ችግር ነው፡፡

እንደዚህ ዓይነት የእይታ ችግር በተለይም ህጻናት የዓይንና አንጎል እድገት ላይ ባለበት በተለይም ዕድሜያቸው ከ8 ዓመት በፊት ጀምሮ ደህና የሚያየውን ዓይን በየቀኑ ለተወሰነ ጊዜ በመሸፈን የማየት ችሎታው የቀነሰውን ዓይን ብቻ እንዲያይ በማስገደድ ዕታው እየበረታ እንዲመጣ በማድረግ ማስተካከል ይቻላል፡፡

፪ የዓይን መንሸዋረር

በቅርብ ማየት በማይችሉ (Hyperopia) ልጆች ላይ የእይታ ችግሩን ተፈጥሯዊ በሆነ መንገድ ለማሻሻል ከሚደረግ ጥረት ጋር ተያይዞ የሚመጣ የመንሸዋረር ዓይነት ሲሆን ሕክምናውም የእይታ ማስተካከያ መነጽር ማድረግ ነው፡፡

፫ የብርሃን መቀበያ (ረቲና) መላቀቅ

ከፍተኛ የሆነ በርቀት የማየት ችግር ያለበቸው ሰዎች ለረቲና መላቀቅ ተጋላጭ ናቸው፡፡

እንደዚህ ዓይነት ችግር ያለባቸው ሰዎች የብርሃን መቀበያው መሳሳትና በቀላሉ እንዲላቀቅ የሚያደርጉ ሌሎች አጋላጫ ነገሮች ስለሚፈጠር የሚከሰት የረቲና መላቀቅ ችግር ነው፡፡

መደበኛ የሆነ ክትትልና አስፈላጊውን ህክምና በማድረግ እንዲሁም የተላቀቀውን ረቲና በወቅቱ በቀዶ ጥገና ማስተካከል ይቻላል፡፡

፬ የዓይን ግፊት ተጋላጭነት

ከሁሉም ዓይነት በመነጽር የሚስተካከል የእይታ ችግር ጋር የሚያያዝ ለዓይን ግፊት መጨመር እንዲሁም የግላኮማ በሽታ ተጋላጭነት ይኖራል፡፡

፭ የዓይን ሞራ

በብዛት በርቀት የማየት ችግር ያለባቸው ሰዎች ላይ ለዓይን ሞራ መፈጠር ተጋላጭ ናቸው፡፡

ስለመነጽር በኅብረተሰቡ ዘንድ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶች

“መነጽር ማድረግ ዓይን እንዲለምደው ያደርጋል”

“መነጽር የዓይን እይታን ያሰንፋል”

“ህጻናት በዚህ እድሜያቸው እንዴት መነጽር ያደርጋሉ፤ ሲያድጉ ቢያደርጉ ይሻላል” የሚሉና የመሳሰሉት ትክክል ያልሆኑ አመለካከቶች መስተካካል ይገባቸዋል፡፡ እነዚህን የመሳሰሉ ጥያቄዎችን ከሚመለከታችው የሕክምና ባለሙያዎች ጋር በመነጋገር ትክክለኛውን ዕውቀት ማግኘት ተገቢ ነው፡፡

ዋቢ መጽሐፍ

የዐይን ጤናና ክብካቤ (2009)

በፕ/ር የሺጌታ ገላው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *